26.The Poets
- ጠ.ሰ.መ. (ጧ ሲን ሚም)፡፡
- ይህች ግልጽ ከኾነው መጽሐፍ አንቀጾች ናት፡፡
- አማኞች ባለመኾናቸው፤ (በቁጭት) ነፍስህን ገዳይ መኾን ይፈራልሃል፡፡
- ብንሻ በእነሱ ላይ ከሰማይ ተዓምረን እናወርድና አንገቶቻቸው (መሪዎቻቸው) ለእርሷ ተዋራጆች ይኾናሉ፡፡
- ከአልረሕማንም ዘንድ ኣዲስ የተወረደ ቁርኣን አይመጣላቸውም፤ ከእርሱ የሚሸሹ ቢኾኑ እንጂ፡፡
- በእርግጥም አስተባበሉ፡፡ የዚያም በእርሱ ይሳለቁበት የነበሩት ወሬዎች (ፍጻሜ) ይመጣባቸዋል፡፡
- ወደ ምድርም በውስጧ ከመልካም (በቃይ) ጎሳ ሁሉ ብዙን እንዳበቀልን አላዩምን፡፡
- በዚህ አስደናቂ ምልክት አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
- ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊ አዛኝ ነው፡፡
- ጌታህም ሙሳን «ወደ በደለኞቹ ሕዝቦች ኺድ» በማለት በጠራው ጊዜ (አስታውስ)፡፡
- «ወደ ፈርዖን ሕዝቦች (ኺድ) አላህን አይፈሩምን» (አለው)፡፡
- (ሙሳም) አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔ ሊያስተባብሉኝ እፈራለሁ፡፡
- «ልቤም ይጠብባል፡፡ ምላሴም አይፈታም፡፡ ስለዚህ ወደ ሃሩን ላክ፡፡
- «ለእነርሱም በእኔ ላይ (የደም) ወንጀል አልለ፡፡ ስለዚህ እንዳይገድሉኝ እፈራለሁ፡፡»
- (አላህ) አለ «ተው! (አይነኩህም)፡፡ በተዓምራቶቻችንም ኺዱ፡፡ እኛ ከእናንተ ጋር ሰሚዎች ነንና፡፡
- «ወደ ፈርዖንም ኺዱ፡፡ በሉትም፡- እኛ የዓለማት ጌታ መልክተኞች ነን፡፡
- «የእስራኤልን ልጆች ከእኛ ጋር ልቀቅ፡፡»
- (ፈርዖንም) አለ «ልጅ ኾነህ በእኛ ውስጥ አላሳደግንህምን በእኛ ውስጥም ከዕድሜህ ብዙ ዓመታትን አልተቀመጥክምን
- «ያችንም የሠራሃትን ሥራህን አልሠራህምን አንተም ከውለታ ቢሶቹ ነህ» (አለ)፡፡
- (ሙሳም) አለ «ያን ጊዜ እኔም ከተሳሳቱት ኾኜ ሠራኋት፡፡
- «በፈራኋችሁም ጊዜ ከእንናተ ሸሸሁ፡፡ ጌታየም ለእኔ ጥበብን ሰጠኝ፡፡ ከመልክተኞቹም አደረገኝ፡፡
- «ይህችም የእስራኤልን ልጆች ባሪያ በማድረግህ በእኔ ላይ የምትመጻደቅባት ጸጋ ነት፡፡»
- ፈርዖን አለ «(ላከኝ የምትለው) የዓለማትም ጌታ ምንድነው»
- (ሙሳ) «የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ጌታ ነው፡፡ የምታረጋግጡ ብትኾኑ (ነገሩ ይህ ነው)፤» አለው፡፡
- (ፈርዖንም) በዙሪያው ላሉት ሰዎች «አትሰሙምን» አለ፡፡
- (ሙሳ) «ጌታችሁና የመጀመሪያዎቹ አባቶቻችሁም ጌታ ነው» አለው፡፡
- (ፈርዖን) «ያ ወደእናንተ የተላከው መልክተኛችሁ በእርግጥ ዕብድ ነው» አለ፡፡
- (ሙሳ) «የምሥራቅና የምዕራብ በመካከላቸውም ያለው ነገር ሁሉ ጌታ ነው፡፡ ታውቁ እንደኾናችሁ (እመኑበት)» አለው፡፡
- (ፈርዖን) «ከእኔ ሌላ አምላክን ብትይዝ በውነቱ ከእስረኞቹ አደርግሃለሁ» አለ፡፡
- (ሙሳ) «በግልጽ አስረጅ ብመጣህም እንኳ» አለው፡፡
- «እንግዲያውስ ከእውነተኞች እንደኾንክ (አስረጁን) አምጣው» አለ፡፡
- በትሩንም ጣለ፡፡ እርሷም ወዲያውኑ ግልጽ እባብ ኾነች፡፡
- እጁንም አወጣ፡፡ ወዲያውም እርሷ ለተመልካቾች (የምታበራ) ነጭ ኾነች፡፡
- (ፈርዖን) በዙሪያው ላሉት መማክርት «ይህ በእርግጥ ዐዋቂ ድግምተኛ ነው» አለ፡፡
- «ከምድራችሁ በድግምቱ ሊያወጣችሁ ይፈልጋልና ምንን ታዛላችሁ» (አላቸው)፡፡
- አሉት «እርሱን ወንድሙንም አቆይና በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን ላክ፡፡
- «በጣም ዐዋቂ ድግምተኞችን ሁሉ ያመጡልሃልና፡፡»
- ድግምተኞቹም በታወቀ ቀን ቀጠሮ ተሰበሰቡ፡፡
- ለሰዎቹም «እናንተ ተሰብስባችኋልን» ተባለ፡፡
- «ድግምተኞቹን እነሱ አሸናፊዎች ቢኾኑ እንከተል ዘንድ» (ተባለ)፡፡
- «ድግምተኞቹም በመጡ ጊዜ ለፈርዖን እኛ አሸናፊዎች ብንሆን ለእኛ በእርግጥ ዋጋ አለን» አሉት፡፡
- «አዎን፤ እናንተም ያን ጊዜ ከባለሟሎቹ ትኾናላችሁ» አላቸው፡፡
- ሙሳ «ለእነርሱ እናንተ የምትጥሉትን ጣሉ» አላቸው፡፡
- ገመዶቻቸውንና በትሮቻቸውንም ጣሉ፡፡ «በፈርዖንም ክብር ይኹንብን፡፡ እኛ በእርግጥ አሸናፊዎቹ እኛ ነን» አሉ፡፡
- ሙሳም በትሩን ጣለ፡፡ ወዲያውም እርሷ የሚያስመስሉትን ሁሉ ትውጣለች፡፡
- ድግምተኞቹም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ፡፡
- (እነሱም) አሉ «በዓለማት ጌታ አመንን፡፡
- «በሙሳና በሃሩን ጌታ፡፡»
- (ፈርዖንም) «ለእናንተ ሳልፈቅድላችሁ በፊት ለእርሱ አመናችሁን እርሱ ያ ድግምትን ያስተማራችሁ ታላቃችሁ ነው፡፡ ወደፊትም (የሚያገኛችሁን) በእርግጥ ታውቃላችሁ፡፡ እጆቻችሁንና እግሮቻችሁን (ቀኝና ግራን) በማናጋት እቆረርጣለሁ፡፡ ሁላችሁንም እሰቅላችኋለሁም» አለ፡፡
- (እነርሱም) አሉ «ጉዳት የለብንም፡፡ እኛ ወደ ጌታችን ተመላሾች ነን፡፡
- «እኛ የምእምናን መጀመሪያ በመኾናችን ጌታችን ኀጢአቶቻችንን ለእኛ ሊምር እንከጅላለን፡፡»
- ወደ ሙሳም «ባሮቼን ይዘህ ሌሊት ኺድ፡፡ እናንተ የሚከተሉዋችሁ ናችሁና» ስንል ላክን፡፡
- ፈርዖንም በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን (እንዲህ ሲል) ላከ፡፡
- «እነዚህ ጥቂቶች ጭፈሮች ናቸው፡፡
- «እነርሱም ለእኛ አስቆጪዎች ናቸው፡፡
- «እኛም ብዙዎች ጥንቁቆች ነን፤» (አለ)፡፡
- አወጣናቸውም፡፡ ከአትክልቶችና ከምንጮች፡፡
- ከድልቦችም ከመልካም መቀመጫዎችም፡፡
- እንደዚሁ ለእስራኤል ልጆች አወረስናትም፡፡
- ፀሐይዋ ስትወጣም ተከተሉዋቸው፡፡
- ሁለቱ ጭፍሮችም በተያዩ ጊዜ የሙሳ ጓዶች «እኛ(የፈርዖን ሰዎች) የሚደርሱብን ነን» አሉ፡፡
- (ሙሳ) «ተዉዉ! ጌታዬ ከእኔ ጋር ነው፡፡ በእርግጥ ይመራኛል» አለ፡፡
- ወደ ሙሳም «ባሕሩን በበትርህ ምታው» ስንል ላክንበት፡፡ (መታውና) ተከፈለም፡፡ ክፍሉም ሁሉ እንደ ታላቅ ጋራ ኾነ፡፡
- እዚያም ዘንድ ሌሎችን አቀረብን፡፡
- ሙሳንም ከእርሱ ገር ያሉትንም ሰዎች ሁሉንም አዳን፡፡
- ከዚያም ሌሎቹን አሰጠምን፡፡
- በዚህ ውስጥ ታላቅ ታምር አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
- ጌታህም እርሱ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- በእነሱም (በሕዝቦችህ) ላይ የኢብራሂምን ወሬ አንብብላቸው፡፡
- ለአባቱና ለሕዝቦቹ «ምንን ትግገዛላችሁ» ባለ ጊዜ፡፡
- «ጣዖታትን እንገዛለን፤ እርሷንም በመገዛት ላይ እንቆያለን» አሉ፡፡
- (እርሱም) አለ «በጠራችኋቸው ጊዜ ይሰሟችኋልን
- «ወይስ ይጠቅሟችኋልን ወይስ ይጎዷችኋልን»
- «የለም! አባቶቻችን እንደዚሁ ሲሠሩ አገኘን» አሉት፡፡
- «ትግገዙት የነበራችሁትን አስተዋላችሁን
- «እናንተም የቀድሞዎቹ አባቶቻችሁም (የተግገዛችሁትን)፡፡»
- «እነሱም (ጣዖቶቹ) ለእኔ ጠላቶች ናቸው፡፡ ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር (እርሱ ወዳጄ ነው)፡፡
- «(እርሱ) ያ የፈጠረኝ ነው፡፡ እርሱም ይመራኛል፡፡
- «ያም እርሱ የሚያበላኝና የሚያጠጣኝ ነው፡፡
- «በታመምኩም ጊዜ እርሱ ያሽረኛል፡፡
- «ያም የሚገድለኝ ከዚያም ሕያው የሚያደርገኝ ነው፡፡
- ያም በፍርዱ ቀን ኀጢአቴን ለእኔ ሊምር የምከጅለው ነው፡፡
- ጌታዬ ሆይ! ዕውቀትን ስጠኝ! በደጋጎቹም ሰዎች አስጠጋኝ፡፡
- በኋለኞቹም ሕዝቦች ውስጥ ለእኔ መልካም ዝናን አድርግልኝ፡፡
- የጸጋይቱን ገነት ከሚወርሱትም አድርገኝ፡፡
- ለአባቴም ማር፡፡ እርሱ ከተሳሳቱት ነበረና፡፡
- በሚቀሰቀሱበት ቀንም አታዋርደኝ፡፡
- ገንዘብም ልጆችም በማይጠቅሙበት ቀን፡፡
- ወደ አላህ በንጹህ ልብ የመጣ ሰው ቢኾን እንጅ፡፡»
- ገነትም ለፈሪዎች በምትቀረብበት (ቀን)፡፡
- ገሀነምም ለጠመሞች በምትገለጽበት (ቀን)፡፡
- ለእነሱም በሚባል ቀን «ትግገዟቸው የነበራችሁት የት ናቸው»
- «ከአላህ ሌላ ሲኾኑ ይረዱዋችኋልን ወይስ (ለራሳቸው) ይርረዳሉን»
- በውስጧም እነሱና ጠማሞቹ በፊቶቻቸው ተጥለው ይንከባለላሉ፡፡
- የሰይጣንም ሰራዊቶች መላውም (ይጣላሉ)፡፡
- እነርሱም በእርሷ ውስጥ የሚከራከሩ ኾነው ይላሉ፡
- በአላህ እንምላለን፤ እኛ በግልጽ መሳሳት ውስጥ ነበርን፡፡
- (ጣዖቶቹን) በዓለማት ጌታ ባስተካከልናችሁ ጊዜ፡፡
- አመጸኞቹም እንጅ ሌላ አላሳሳተንም፡፡
- ከአማላጆችም ለእኛ ምንም የለንም፡፡
- አዛኝ ወዳጂም (የለንም)፡፡
- ለእኛም አንዲት ጊዜ መመለስ በኖረችንና ከአማኞቹ በኾን እንመኛለን (ይላሉ)፡፡
- በዚህ ውስጥ አስደናቂ ግሳጼ አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
- ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- የኑሕ ሕዝቦች መልክተኞችን አስተባበሉ፡፡
- ወንድማቸው ኑሕ ለእነሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
- «እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
- «አላህንም ፍሩ ታዘዙኝም፡፡
- «በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
- «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡»
- (እነርሱም) «ወራዶቹ የተከተሉህ ኾነህ ለአንተ እናምናለን» አሉት፡፡
- (እርሱም) አላቸው «ይሠሩት በነበሩት ነገር ምን ዕውቀት አለኝ፡፡
- «ምርመራቸው በጌታዬ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡ ብታውቁ ኖሮ (ይህንን ትርረዱ ነበር)፡፡
- «እኔም አማኞችን አባራሪ አይደለሁም፡፡
- «እኔ ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም፡፡»
- «ኑሕ ሆይ! (ከምትለው) ባትከለከል በእርግጥ ከሚወገሩት ትኾናለህ» አሉት፡፡
- (እርሱም) አለ «ጌታዬ ሆይ! ሕዝቦቼ አስተባበሉኝ፡፡
- «በእኔና በእነርሱም መካከል (ተገቢ) ፍርድን ፍረድ፡፡ አድነኝም፡፡ ከእኔ ጋር ያሉትንም ምእምናን፡፡»
- እርሱንም ከእርሱ ጋር ያለውንም ሁሉ በተመላው መርከብ ውስጥ አዳን፡፡
- ከዚያም በኋላ ቀሪዎቹን አሰጠምን፡፡
- በዚህ ውስጥ ታላቅ ግሳጼ አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
- ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- ዓድ መልክተኞችን አስተባበለች፡፡
- ወንድማቸው ሁድ ለነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
- «እኔ ለናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
- «አላህንም ፍሩ ታዘዙኝም፡፡
- «በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
- «የምትጫወቱ ኾናችሁ በከፍተኛ ስፍራ ሁሉ ላይ ምልክትን ትገነባላችሁን
- «የውሃ ማጠራቀሚያዎችንና ሕንፃዎችንም ዘላለም መኖርን የምትከጅሉ ኾናችሁ ትሠራላችሁን
- «በቀጣችሁም ጊዜ ጨካኞች ኾናችሁ ትቀጣላችሁን
- «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
- «ያንንም በምታውቁት (ጸጋ) ያጣቀማችሁን ፍሩ፡፡
- «በእንስሳዎችና በልጆች ያጣቀማችሁን፡፡
- «በአትክልቶችና በምንጮችም፡፡
- «እኔ በእናንተ ላይ የታላቅን ቀን ቅጣት እፈራለሁና፡፡»
- (እነርሱም) አሉ «ብትገስጽም ወይም ከገሳጮቹ ባትኾንም በእኛ ላይ እኩል ነው፤ (ያለንበትን አንለቅም)፡፡
- «ይህ የፊተኞቹ ሰዎች ፀባይ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡
- «እኛም የምንቅቀጣ አይደለንም» (አሉ)፡፡
- አስተባበሉትም፡፡ አጠፋናቸውም፡፡ በዚህም ውስጥ እርግጠኛ ግሳጼ አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡
- ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- ሰሙድ መልክተኞችን አስተባበለች፡፡
- ወንድማቸው ሷሊህ ለእነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
- «እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
- «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
- «በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
- «በዚያ እዚህ ባለው (ጸጋ) ውስጥ የረካችሁ ኾናችሁ ትተዋላችሁን
- «በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ፡፡
- «በአዝመራዎችም ፍሬዋ የበሰለ በኾነች ዘንባባም፤ (ውስጥ ትተዋላችሁን)
- «ብልሆች ኾናችሁ ከጋራዎች ቤቶችንም ትጠርባላችሁ፡፡
- «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
- «የወሰን አላፊዎችንም ትዕዛዝ አትከተሉ፡፡
- «የእነዚያን በምድር ላይ የሚያጠፉትንና የማያበጁትን፡፡»
- (እነሱም) አሉ «አንተ በብዙ ከተደገመባቸው ሰዎች ብቻ ነህ፡፡
- «አንተ ብጤያችን ሰው እንጅ ሌላ አይደለህም፡፡ ከእውነተኞቹም እንደኾንክ ተዓምርን አምጣ፡፡»
- (እርሱም) አለ «ይህች ግመል ናት፡፡ ለእርሷ የመጠጥ ፋንታ አላት፡፡ ለእናንተም የታወቀ ቀን ፋንታ አላችሁ፡፡
- «በክፉም አትንኳት፡፡ የታላቅ ቀን ቅጣት ይይዛችኋልና፡፡»
- ወጓትም፡፡ ወዲያውም ተጸጻቾች ኾነው አነጉ፡፡
- ቅጣቱም ያዛቸው፡፡ በዚህም ውስጥ ግሳፄ አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡
- ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- የሉጥ ሕዝቦች መልክተኞችን አስተባባሉ፡፡
- ወንድማቸው ሉጥ ለእነርሱ ባለ ጊዜ «አትጠነቀቁምን
- «እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
- «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
- «በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
- «ከዓለማት ሰዎች ወንዶችን ትመጣላችሁን
- «ከሚስቶቻችሁም ጌታችሁ ለናንተ የፈጠረላችሁን ትተዋላችሁን በእውነቱ እናንተ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦ ናችሁ፡፡»
- (እነርሱም) አሉ «ሉጥ ሆይ! ባትከለከል በእርግጥ (ከአገር) ከሚወጡት ትኾናለህ፡፡»
- (እርሱም) አለ «እኔ ሥራችሁን ከሚጠሉት ሰዎች ነኝ፡፡
- «ጌታዬ ሆይ! እኔንም ቤተሰቦቼንም ከሚሠሩት ሥራ (ቅጣት) አድነን፡፡»
- እርሱንም ቤተሰቦቹንም በጠቅላላ አዳንናቸው፡፡
- በቀሪዎቹ ውስጥ የኾነች አሮጊት ብቻ ስትቀር (እርሷ ጠፋች)፡፡
- ከዚያም ሌሎቹን አጠፋን፡፡
- በእነሱም ላይ (የድንጋይን) ዝናምን አዘነምንባቸው፡፡ የተስፈራሪዎቹም ዝናም (ምንኛ) ከፋ፡፡
- በዚህ ውስጥ አስደናቂ ተዓምር አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡
- ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- የአይከት ሰዎች መልክተኞችን አስተባበሉ፤
- ሹዕይብ ለእነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
- «እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
- «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
- «በርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
- «ስፍርን ሙሉ፡፡ ከአጉዳዮቹም አትኹኑ፡፡
- «በትክክለኛ ሚዛንም መዝኑ፡፡
- «ሰዎችንም ነገሮቻቸውን አታጉድሉባቸው፡፡ በምድርም ላይ አጥፊዎች ኾናችሁ አታበላሹ፡፡
- «ያንንም የፈጠራችሁን የቀድሞዎቹንም ፍጡሮች (የፈጠረውን) ፍሩ፡፡»
- አሉ «አንተ በብዛት ከተደገመባቸው ሰዎች ነህ፡፡
- «አንተም ብጤያችን ሰው እንጅ ሌላ አይደለህም፡፡ እነሆ ከውሸታሞች ነህ ብለን እንጠረጥርሃለን፡፡
- «ከእውነተኞቹም እንደኾንክ በእኛ ላይ ከሰማይ ቁራጭን ጣልብን፡፡»
- «ጌታዬ የምትሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው፤» አላቸው፡፡
- አስተባበሉትም፡፡ የጥላይቷ ቀን ቅጣትም ያዛቸው፡፡ እርሱ የከባድ ቀን ቅጣት ነበርና፡፡
- በዚህ ውስጥ አስደናቂ ተዓምር አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእምናን አልነበሩም፡፡
- ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- እርሱም (ቁርኣን) በእርግጥ ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡
- እርሱን ታማኙ መንፈስ (ጂብሪል) አወረደው፤
- ከአስፈራሪዎቹ (ነቢያት) ትኾን ዘንድ በልብህ ላይ (አወረደው)፡፡
- ግልጽ በኾነ ዐረብኛ ቋንቋ፡፡
- እርሱም (ቁርኣን) በቀድሞዎቹ መጻሐፍት ውስጥ (የተወሳ ነው)፡፡
- የእስራኤል ልጆች ሊቃውንት የሚያውቁት መኾኑ ለእነርሱ (ለመካ ከሓዲዎች) ምልክት አይኾናቸውምን
- ከአዕጀሞች ባንዱ ላይ ባወረድነውም ኖሮ፤
- በእነርሱ ላይ ባነበበውም በእርሱ አማኞች አይኾኑም ነበር፡፡
- እንደዚሁ (ማስተባበልን) በተንኮለኞች ልቦች ውስጥ አስገባነው፡፡
- አሳማሚ ቅጣትን እስከሚያዩ ድረስ በእርሱ አያምኑም፡፡
- እነርሱ የማያውቁ ሲኾኑ (ቅጣቱ) ድንገት እስከሚመጣባቸውም ድረስ (አያምኑም)፡፡
- (በመጣባቸው ጊዜ) «እኛ የምንቆይ ነን» እስከሚሉም (አያምኑም)፡፡
- በቅጣታችን ያቻኩላሉን
- አየህን ብዙ ዓመታትን ብናጣቅማቸው፤
- ከዚያም ያ ይስፈራሩበት የነበሩት ቢመጣባቸው፤
- ይጣቀሙበት የነበሩት ሁሉ ከእነሱ ምንም አያብቃቃቸውም፡፡
- አንዲትንም ከተማ ለእርሷ አስፈራሪዎች ያሏት (እና ያስተባበለች) ኾና እንጅ አላጠፋንም፡፡
- (ይህች) ግሳፄ ናት፡፡ በዳዮችም አልነበርንም፡፡
- ሰይጣናትም እርሱን (ቁርኣንን) አላወረዱትም፡፡
- ለእነርሱም አይገባቸውም፤ አይችሉምም፡፡
- እነርሱ (የመላእክትን ንግግር) ከመስማት ተከለከሉ ናቸው፡፡
- ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አትግገዛ፤ ከሚቀጡት ትኾናለህና፡፡
- ቅርቦች ዘመዶችህንም አስጠንቅቅ፡፡
- ከምእምናንም ለተከተሉህ ሰዎች ክንፍህን ዝቅ አድርግ፤ (ልዝብ ኹን)፡፡
- «እንቢ» ቢሉህም «እኔ ከምትሠሩት ንጹሕ ነኝ» በላቸው፡፡
- አሸናፊ አዛኝ በኾነው (ጌታህ) ላይም ተጠጋ፡፡
- በዚያ ለሶላት በምትቆም ጊዜ በሚያይህ፡፡
- በሰጋጆች ውስጥ መዘዋወርህንም (በሚያየው ጌታህ ላይ ተጠጋ)፡፡
- እነሆ እርሱ ሰሚው ዐዋቂው ነውና፡፡
- ሰይጣናት በማን ላይ እንደሚወርዱ ልንገራችሁን
- በውሸታም ኀጢአተኛ ሁሉ ላይ ይወርዳሉ፡፡
- የሰሙትን (ወደ ጠንቋዮች) ይጥላሉ፡፡ አብዛኞቻቸውም ውሸታሞች ናቸው፡፡
- ባለ ቅኔዎችንም ጠማማዎቹ ይከተሉዋቸዋል፡፡
- እነርሱ በ(ንግግር) ሸለቆ ሁሉ የሚዋልሉ መኾናቸውን አታይምን
- እነሱም የማይሠሩትን ነገር የሚናገሩ መኾናቸውን (አታይምን)፤
- እነዚያ ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ አላህንም በብዛት ያወሱ ከተበደሉም በኋላ (በቅኔ) የተከላከሉ ሲቀሩ፤ (እነርሱ አይወቀሱም)፡፡ እነዚያም የበደሉ (ከሞቱ በኋላ) እንዴት ያለን መመለስ እንደሚመለሱ በእርግጥ ያውቃሉ፡፡